Deuteronomy 2

በምድረ በዳ መንከራተት

1ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘኝ መሠረት ተመለስን፤ ቀይ ባሕርን
ዕብራይስጡ፣ ያም ሳውፍ ይለዋል፤ ይኸውም የደንገል ባሕር ማለት ነው።
ይዘን ወደ ምድረ በዳው ተጓዝን፤ በሴይር ኰረብታማ አገር ዙሪያ ለረጅም ጊዜ ተንከራተትን።

2ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤ 3“በዚህ በኰረብታማ አገር ዙሪያ እስኪበቃችሁ ተንከራታችኋል፤ አሁን ግን ወደ ሰሜን ተመለሱ። 4ለሕዝቡም እነዚህን ትእዛዞች ስጣቸው፤ ሴይር በሚኖሩት በወንድሞቻችሁ በዔሳው ዘሮች ግዛት ዐልፋችሁ ትሄዳላችሁ፤ እነርሱ ይፈሯችኋል፤ ቢሆንም ከፍ ያለ ጥንቃቄ አድርጉ። 5ከየትኛውም ምድራቸው ላይ ለጫማችሁ መርገጫ ታህል እንኳ መሬት ስለማልሰጣችሁ፣ ለጦርነት አታነሣሷቸው። ኰረብታማውን የሴይርን አገር ርስት አድርጌ ለዔሳው ሰጥቼዋለሁ። 6ከዚያ ለምትበሉት ምግብም ሆነ ለምትጠጡት ውሃ በጥሬ ብር ትከፍሏቸዋላችሁ።”

7አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጃችሁ ሥራ ሁሉ ባርኳችኋል፤ በዚህ ጭልጥ ባለው ምድረ በዳ ባደረጋችሁት ጕዞ ጠብቋችኋል። በእነዚህ አርባ ዓመታት አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከእናንተ ጋር ነበርና አንዳችም ነገር አላጣችሁም።

8ስለዚህ በሴይር የሚኖሩ የዔሳው ዘሮች የሆኑ ወንድሞቻችንን ዐልፈናቸው ሄድን። ከኤላትና ከዔጽዮንጋብር ከሚመጣው ከዓረባ መንገድ ተመልሰን፣ በሞዓብ ምድረ በዳ መንገድ ተጓዝን።

9ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “ከሞዓባውያን ምድር አንዳችም መሬት ስለማልሰጣችሁ አታስቸግሯቸው፤ ለጦርነትም አታነሣሷቸው፤ ዔርን ለሎጥ ዘሮች ርስት አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ” አለኝ።

10በዚያም ጠንካራና ቍጥራቸው የበዛ እንዲሁም እንደ ዔናቃውያን ረጃጅም የሆኑ ኤሚማውያን ይኖሩ ነበር። 11እነዚህም እንደ ዔናቃውያን ሁሉ ራፋይማውያን ናቸው ተብለው ይገመቱ ነበር፤ ሞዓባውያን ግን ኤሚማውያን ብለው ይጠሯቸዋል። 12ሖራውያን ቀድሞ በሴይር ይኖሩ ነበር፤ የዔሳው ዘሮች ግን ከዚያ አሳድደው አስወጧቸው። እግዚአብሔር (ያህዌ) ርስት አድርጎ በሰጠው ምድር ላይ እስራኤል እንዳደረገው ሁሉ፣ እነዚህም ሖራውያንን ከፊታቸው አጥፍተው መኖሪያቸውን እዚያው አደረጉ።

13ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) “አሁኑኑ ተነሡና የዘሬድን ደረቅ ወንዝ ተሻገሩ” አለን፤ እኛም ወንዙን ተሻገርን።

14ቃዴስ በርኔን ከለቀቅንበት ጊዜ አንሥቶ የዘሬድን ደረቅ ወንዝ እስከ ተሻገርንበት ጊዜ ድረስ ሠላሳ ስምንት ዓመት ዐለፈ። በዚያን ጊዜም ለጦርነት ብቁ የሆኑት የዚያ ትውልድ ወንዶች ሁሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እነርሱ አስቀድሞ በማለው መሠረት ከሰፈሩ ፈጽመው ዐለቁ። 15ከሰፈር ፈጽሞ እስኪያጠፋቸውም ድረስ የእግዚአብሔር (ያህዌ) እጅ በእነርሱ ላይ ነበር።

16በሕዝቡ መካከል የነበሩት የመጨረሻዎቹ ተዋጊዎች ከሞቱ በኋላ፣ 17እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤ 18“የሞዓብ ዳርቻ ዔርን ዛሬውኑ ታልፋላችሁ። 19ከየትኛውም የአሞናውያን ምድር ለእናንተ ርስት ስለማልሰጣችሁ፣ አሞናውያን ዘንድ በደረሳችሁ ጊዜ አታስቸግሯቸው፤ ለጦርነትም አታነሣሷቸው። ያን ቦታ ርስት አድርጌ ለሎጥ ዘሮች ሰጥቻቸዋለሁ።”

20ያም ደግሞ በዚያ ይኖሩ የነበሩት የረፋይማውያን ምድር እንደ ሆነ ይቈጠር ነበር፤ አሞናውያን ግን ዘምዙማውያን ብለው ይጠሯቸው ነበር። 21ዘምዙማውያን ብርቱዎች፣ ቍጥራቸው የበዛና እንደ ዔናቃውያን ቁመተ ረጃጅሞች ነበሩ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእነርሱ ፊት አጠፋቸው፤ እነርሱም አሳደዷቸው፤ በምትካቸውም ሰፈሩበት።

22 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሖራውያንን ከፊታቸው ባጠፋ ጊዜ፣ በሴይር ለሚኖሩት የዔሳው ዘሮች ያደረገው ይህንኑ ነበር። እነርሱም አሳድደው በማስወጣት ባስለቀቁት ስፍራ ላይ እስከ ዛሬ ይኖራሉ። 23እስከ ጋዛ ድረስ ባሉት መንደሮች የኖሩትን ኤዋውያን በተመለከተም፣ ከከፍቶር
ቀርጤስ ነች
ወጥተው የመጡት ከፍቶራውያን፣ እነርሱን አጥፍተው መኖሪያቸውን እዚያው አደረጉ።

የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎን ድል መነሣት

24“አሁኑኑ ተነሡና የአርኖንን ወንዝ ተሻገሩ፤ እነሆ፤ የሐሴቦንን ንጉሥ፣ አሞራዊውን ሴዎንንና አገሩን በእጃችሁ ሰጥቻችኋለሁ፤ ምድሩን መውረስ ጀምሩ፤ ጦርነት ግጠሙት። 25ከሰማይ በታች ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ፣ ማስደንገጣችሁና ማስፈራታችሁ እንዲያድርባቸው ከዚህች ከዛሬዋ ዕለት እጀምራለሁ። ስለ እናንተ ሰምተው ይርበተበታሉ፤ ከእናንተ የተነሣም ይጨነቃሉ።”

26ከቅዴሞት ምድረ በዳም ለሐሴቦን ንጉሥ ለሴዎን የሰላም ቃል እንዲያደርሱለት እንዲህ በማለት መልእክተኞች ላክሁ፤ 27“በአገርህ አቋርጠን እንድናልፍ ፍቀድልን፤ ከዋናው መንገድ አንወጣም፤ ቀኝም ግራም አንልም። 28የምንበላውን ምግብ፣ የምንጠጣውንም ውሃ በጥሬ ብር ሽጥልን። በእግር እንድናልፍ ብቻ ፍቀድልን፤ 29በሴይር የሚኖሩ የዔሳው ዘሮችና በዔር የሚኖሩ ሞዓባውያን እንዳደረጉልን ሁሉ፣ አንተም አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጠን ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን እስክንሻገር ድረስ እንደዚሁ አድርግልን።” 30ይሁን እንጂ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎን እንድናልፍ አልፈቀደልንም፤ ምክንያቱም አምላካችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ ኤሎሂም) አሁን እንዳደረገው ሁሉ እርሱን በእጃችሁ አሳልፎ ለመስጠት መንፈሱን አደንድኖት፣ ልቡንም አጽንቶት ነበር።

31 እግዚአብሔርም (ያህዌ)፣ “እነሆ፤ ሴዎንንና አገሩን ለእናንተ አሳልፌ ልሰጣችሁ ተነሥቻለሁ፤ አሁንም እርሱን አሸንፋችሁ ምድሩን ለመውረስ ተነሡ” አለኝ።

32ሴዎንና መላው ሰራዊቱ በያሀጽ ጦርነት ሊገጥሙን በወጡ ጊዜ፣ 33አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጃችን ላይ ጣለው፤ እኛም፣ እርሱን ከወንድ ልጆቹና ከመላው ሰራዊቱ ጋር አንድ ላይ መታነው። 34በዚያን ጊዜ ከተሞቹን በሙሉ ወስደን የሚኖሩባቸውን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆቻቸውን ጭምር ፈጽመን አጠፋናቸው
የዕብራይስጡ ቃል አንድን ነገር ወይም አንድን ሰው ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠትን የሚያሳይ ነው።
፤ አንዳቸውንም በሕይወት አላስቀረንም።
35ከብቶቻቸውንና ከየከተሞቻቸው ያገኘነውን ምርኮ ግን ለራሳችን አደረግን። 36በአርኖን ሸለቆ ጫፍ ካለችው ከአሮዔርና በሸለቆው ውስጥ ከምትገኘዋ ከተማ አንሥቶ እስከ ገለዓድ ካሉት ከተሞች አንዳቸውም እንኳ ሊገቱን አልቻሉም። አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሁሉንም አሳልፎ ሰጠን። 37ይሁን እንጂ አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጠው ትእዛዝ መሠረት፣ ወደ ማናቸውም የአሞናውያን ምድር ወይም በያቦቅ ወንዝ መውረጃ ወዳለው ምድር ወይም ደግሞ በኰረብቶች ወዳሉት ከተሞች ዙሪያ ዐልፋችሁ አልሄዳችሁም።

Copyright information for AmhNASV